በተለያዩ የአለም ክፍል የፋሲካ በዓል ለምን በተለያዬ ጊዜ ይከበራል?
ምን አልባት እርስዎ ለፋሲካ በዓል የሚያስፈልጉ ምግብና መጠጦችን እየሸመቱ፤ እያሰነዳዱ ይሆናል። ሌሎች ግን ያዘጋጇቸውን ምግቦች ተመግበው የፋሲካ ደስታቸውን አጣጥመው የጨረሱት የዛሬ ሳምንት ነው።
በዓለማችን የሚገኙ የተለያዩ አገራት የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች የፋሲካን በዓል ባለፈው ሳምንት እሁድ አክብረው አልፈዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገራት ደግሞ የፋሲካን በዓል ነገ እሁድ ለማክበር ዋዜማው ላይ ይገኛሉ።
በአውሮፓ ፣ አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በምዕራቡ ዓለም ካሉት የእምነቱ ተከታዮች በአንድ ሳምንት ዘግይተው ነው በዓሉን የሚያከብሩት። ለመሆኑ ይህ ለምን ሆነ?
ፋሲካ የክርስትያን በዓል ሲሆን የእምነቱ ተከታዮች ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት ዕለት አስበውት ይውላሉ።
በዓሉም ትንሳኤ በመባልም ይጠራል። ይህ በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ወሳኙ በዓል ነው።
በምሥራቁ የኦርቶዶክስ ክርስትያን ዘንድ የዚህ በዓል ዝግጅት የሚጀመረው ለ40 ቀናት በሚቆየው የዐቢይ ጾም ሲሆን፣ ይህ ጾም በንጹህ ሰኞ ( ክሊን መንደይ) ተጀምሮ የፋሲካ ቅዳሜ ይጠናቀቃል።
ንጹሕ ሰኞ አማኞች በዐቢይ ጾም ከኃጢያታቸው መጽዳታቸውን የሚያመለክት ነው። ከፋሲካ ስምንት ቀናት ቀደም ብሎ ያለው ቅዳሜ ደግሞ ታላቁ የዐቢይ ጾም መገባደዱን ይጠቁማል።
ይኹን እንጂ ጾሙ እስከ ፋሲካ ድረስ ይቀጥላል።
ከፋሲካ በዓል ከመከበሩ አንድ ሳምንት በፊት ያለውን ቅዳሜ ተከትሎ ዘንባባ የሚታሰርበት የሆሳዕና በዓል ይከተላል። ይህ ዕለት ሰዎች ከዘንባባ የተሰሩ ቀለበቶችን በማጥለቅ እና ራሳቸው ላይ ዘንባባ በማሰር ኢየሱስ ክርስቶስ ኢየሩሳሌም የገባበትን ዕለት ያስባሉ።
ከዚያም ቅዱሱ ሳምንት ተከትሎ በፋሲካ ዕለት እሁድ ይጠናቀቃል።
በዓሉ የሚከበርበት ቀናት ለምን ተለያየ?
በዓለም ላይ ፋሲካ በተለያየ ቀን ነው ተከብሮ የሚውለው። በየዓመቱ በተመሳሳይ ቀን አይከበርም። ይህ ማለት እንደ የገና በዓል ቁርጥ ያለ ቀን የለውም ማለት ነው።
እንደ ግሪክ፣ ሳይፕረስ እና ሮማኒያ ያሉ አንዳንድ አገራት የፋሲካን በዓል የሚያከብሩት የጁሊያን የቀን መቁጠሪያ ላይ ተመስርተው ነው።
የጁሊያን የዘመን አቆጣጠር ከክርስቶስ ልደት በፊት በ45 በጁሊየስ ቄሳር የተዘጋጀ ነው። ይህ የዘመን አቆጣጠር ፀሐይ በምድር ዙሪያ ለመዞር የሚፈጅባት ጊዜ ላይ ተመስርቶ የተሰራ ነው።
የግሪጎሪያን አቆጣጠር ደግሞ በጳጳስ ግሪጎሪ በ1582 የተዘጋጀ ሲሆን የሥነ ፈለክ ጥናት ትክክለኛ እየሆነ በመምጣቱ በጁሊያን ዘመን አቆጣጠር ላይ ያሉትን አንዳንድ ጉድለቶች ለማስተካከል የተሰራ ነው።
ታላቋ ብሪታንያም በ1752 የዘመን አቆጣጠሯን ወደ ግሪጎሪያን ዘመን አቆጣጠር ለውጣለች።
በመሆኑም የዓለም አገራት በዓሉን በተለያየ ቀን የሚያከብሩት የሚከተሉት የቀን አቆጣጠር ስለሚለያይ እንጂ ሌላ ምክንያት የለውም።
በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ በዓሉ እንዴት ይከበራል?
በዚህ በዓል የእምነቱ ተከታዮች ወደ ቤተክርስትያን በመሄድ በመጸለይ ፣ በመስገድ፣ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በመስማት ያከብራሉ። ወሳኝ የሆነው ጊዜም ከስቅለት ዕለት (አርብ) ይጀምራል።
ወሳኙ ጸሎት የሚደረግበትም በፋሲካ ሌሊት ነው። በኢትዮጵያ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ይህንን ሌሊት የሚያሳልፉት በቤተክርሰቲያን ነው።
በቤተክርስቲያን ደወል ይደወላል፤ ኢየሱስ ክርስቶስን ሞትን ድል አድርጎ መነሳት ለማክበርም ርችት ይተኮሳል።
ከዚህ በኋላ ያሉትና ጾሙ ከተፈሰከ በኋላ ያሉት ክንውኖች ግን ብዙውን ጊዜ በምግብ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብዛኛው የእምነቱ ተከታዮች በተለይ ያከፈሉ ሰዎች (ለቀናት የጾሙ አማኞች) ጾማቸውን የሚፈስኩት በተልባ አሊያም በለስላሳ ምግቦች ነው። ከዚያም ዶሮ ወጥ ይከተላል። ፋሲካን በዶሮ ወጥ መፈሰክ የተለመደ ነው።
ከዚያም እንደየ ባህሉ እና አካባቢው የበግ ሥጋ ፣ ክትፎ፣ ጥብስ፣ ዳቦው፤ ከመጠጡም ጠጁ፣ ጠላው ይከተላል።
ጎረቤት እና ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ በደስታ በዓሉን ያሳልፋሉ።
በግሪክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በባህላዊ መንገድ የተጠበሰ የበግ ስጋ እና ጣፋጭ የትንሳኤ ዳቦን ይመገባሉ።
ጾማቸውን የሚፈቱትም ማግሪቲሳ በሚባል ባህላዊ ሾርባ ነው።
ማግሪቲሳ ከበግ ስጋ፣ ሩዝ እና ከቅመማ ቅመም የተዘጋጀ ሾርባ ነው። በሌሎች ምግቦች ከመፈሰካቸው በፊት የሚወስዱት ምግብ ነው። በኢትዮጵያ ተልባ እና ሌሎች ለስላሳ ምግቦች እንደሚወሰዱት ሁሉ ማለት ነው።
በሰርቢያ የኦርቶዶክስ አማኞች ደግሞ የምግብ ፍላጎትን የሚጨምሩ (አፒታይዘር) ከዚያም በተጠበሰ ስጋ ፣ ቺዝ ፣ የተቀቀለ እንቁላል እና ቀይ ወይን ይፈስካሉ።
በሰርቢያ ከዶሮ የተሰራ ኑድል ወይም የበግ ስጋ እና የአትክልት ሾርባ ወሳኝ የፋሲካ ምግቦች ናቸው።
በሩሲያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ደግሞ ጾማቸውን የሚፈቱት ባህላዊ በሆነ ፓስካ ኬክ ነው።
በምዕራቡ ዓለም ቤተክርስትያን እንቁላል የፋሲካ እና የአዲስ ሕይወት ምልክት ነው።
በመሆኑም በፋሲካ ዕለት ለሰው ልጆች መዳን ሲል በመስቀል ላይ የፈሰሰውን የእየሱስ ክርስቶስን ደም ለመወከል እንቁላሎች ቀይ ቀለም ይቀባሉ።