“ሴቶች በሚጥል በሽታ ሲወድቁ፣ ወንዶቹ ጠብቀው ይደፍሯቸዋል”

“ብዙ ሴቶችን ሕመሙ ሲጥላቸው፣ ወንዶች ጠብቀው ይደፍዋል”

“በገጠር በሚጥል ሕመም የሚሰቃዩ እህቶቼ ብዙዎቹ የሚደርስባቸው ነገር ልብ ይሰብራል፡፡ በተለይ እንጀራ ሲጋግሩና ምግብ ሲያበስሉ ቃጠሎ ይደርስባቸዋል። የአንዳንዶቹ ግማሸ ፊታቸው በእሳት ተለብልቦ አይቻለሁ።”

የበሽታው አስከፊነት፣ ታማሚው የትና መቼ እንደሚወደቅ አለማወቁ ነው፤ ሕይወት ደግሞ መቀጠል አለበት፡፡

በገጠር የሴቶች ሕይወት ጓዳ ነው የሚያልፈው፡፡ እዚያ ደግሞ እሳት አለ፡፡ ሲጥላቸው እሳት ላይ ይወድቃሉ፡፡

በገጠር ሆስፒታሎች ስትዘዋወር በእሳት መለብለብ ደርሶባቸው የቀዶ ሕክምና ክፍል ውስጥ የገቡት ብዙዎቹ የሚጥል ሕመም ታማሚዎች ናቸው፡፡

ያውም እነዚህ ዕድለኛ ታማሚዎች ናቸው፡፡ ቤተሰባቸው የተማረና ንቃት ኖሮት፣ በሽታውን ከእርግማን ጋር ሳያይዙት ሆስፒታል ለመውሰድ የደፈሩ ናቸው፡፡

እናት ብዙ ሴቶችን እሳት ላይ ወድቀው ፊታቸው ተለብልቦ ጎብኝታቸዋለች፡፡

ፊታቸውን እሳት ሲበላው ደግሞ የሚጥለው በሽታ ላይ ሌላ የሕይወታቸው ምስቅልቅሎሽ ይከተላል።

እናት፣ በአንድ ወቅት ጅማ አካባቢ ያጋጠመቻት ልጅ እስከዛሬም ከአእምሮዋ ጓዳ አልተፋቀችም፡፡

“ልጅቷ የሚጥል በሽታ ነበረባት፤ እሳት ላይ ወደቀች፡፡ ፊቷ ጨርሶውኑ ተለብልቦ ማንነቷን መለየት እስኪያቅት ድረስ መልከ-ልውጥ (disfigured) ሆነች፡፡

ልጅቷ ታሪኳን ስትነግረኝ ‘አውቶቡስ ላይ ሁሉ አይጭኑኝም’ አለችኝ፡፡

‘ተሳፋሪ እየለመነልኝ ነው እንጂ ፊቴ በጣም ስለሚያስፈራ አውቶብስ ላይ አይጭኑኝም’ አለችኝ።

የሷ ሁኔታ ልቤን ሰበረው፡፡

በሚጥል በሽታ ሆነው፣ በሕይወት ከተረፉ እንኳ የዘላለም ቁስል ይዘው ነው የሚኖሩት፡፡ ከዚህ በላይ ምን ልብ የሚሰብር ነገር አለ?

እናት እውነቱ የጅማዋ ልጅ ጉዳት የመጨረሻው ስቃይ መስሏት ነበር፡፡

ወደ ገጠር ስትጓዝ ከዚህም የባሰ እንዳለ አወቀች፡፡

“ሚዛን አካባቢ ልናስተምር ሄደን እዛ ያሉ ነርሶች አንድ የሚያስደነግጥ ነገር ነገሩኝ፡፡ የሚጥል ሕመም ያለባቸው ሴቶች፣ የወሊድ መከላከያም አብሮ መውሰድ አለባቸው አሉኝ፡፡

“ለምን?” ብዬ ብጠይቅ ጊዜ ምክንያቱም እኛ ጋ የሚመጡት ብዙዎቹ ማን እንዳስረገዛቸው እንኳን አያውቁም፤ ወንዶች ሕመሙ ሲጥላቸው ጠብቀው ይደፍሯቸዋል” አሉኝ፡፡

“ተደፍረው ያረግዛሉ፤ ሲጨንቃቸው ወልደው መንገድ ላይ ይጥሏቸዋል።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *